መጽሐፍ ቅዱስ

ትንቢተ ሚልክያስ


ምዕራፍ :


Malachi

ምዕራፍ 1።

1፤ በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው።

2፤ ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን። በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤

3፤ ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው።

4፤ ኤዶምያስ። እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ። የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል።

5፤ ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም። እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን ትላላችሁ።

6፤ እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተም። ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? ብላችኋል።

7፤ በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ። እናንተም። ያረከስንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው በማለታችሁ ነው።

8፤ ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

9፤ አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

10፤ በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

11፤ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

12፤ እናንተ ግን። የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው፤ ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው በማለታችሁ አስነቀፋችሁት።

13፤ እናንተ። እነሆ፥ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፤ እንዲሁ ቍርባንን ታመጣላችሁ፤ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን? ይላል እግዚአብሔር።

14፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን።