መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ


ምዕራፍ :


1Kings

ምዕራፍ 1።

1፤ ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር።

2፤ ባሪያዎቹም። ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት።

3፤ በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ።

4፤ ቈንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፥ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር።

5፤ የአጊትም ልጅ አዶንያስ። ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ።

6፤ አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ። እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ አልተቈጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር።

7፤ ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፥ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር።

8፤ ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኃያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም።

9፤ አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ።

10፤ ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።

11፤ ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት። ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን?

12፤ አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ።

13፤ ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው።

14፤ እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።

15፤ ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር።

16፤ ቤርሳቤህም አጐንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም። ምን ትፈልጊያለሽ? አለ።

17፤ እርስዋም አለችው። ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤

18፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤

19፤ እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።

20፤ አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዓይን ይመለከትሃል።

21፤ ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቈጠራለን።

22፤ እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ።

23፤ ለንጉሡም። እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ።

24፤ ናታንም አለ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ። ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን?

25፤ እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ። አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ።

26፤ ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም።

27፤ በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?

28፤ ንጉሡም ዳዊት። ቤርሳቤህን ጥሩልኝ ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች።

29፤ ንጉሡም። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን!

30፤ በእውነት። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ ብሎ ማለ።

31፤ ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና። ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር አለች።

32፤ ንጉሡም ዳዊት። ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ።

33፤ ንጉሡም አላቸው። የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤

34፤ በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ።

35፤ በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።

36፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ ያበጅ ያድርግ፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር።

37፤ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፥ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ።

38፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።

39፤ ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ አሉ።

40፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።

41፤ አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድር ነው? አለ።

42፤ እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም። አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ አለ።

43፤ ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ። በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው።

44፤ ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት።

45፤ ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው።

46፤ ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል።

47፤ የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ።

48፤ ንጉሡም ደግሞ። ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ።

49፤ አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ።

50፤ አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ።

51፤ ለሰሎሞንም። እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ። ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል አሉት።

52፤ ሰሎሞንም። እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል አለ።

53፤ ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም። ወደ ቤትህ ሂድ አለው።