የካንሣስ ደብረ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ታሪክ

ስለ ካንሣስ ደብረ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አመሰራረትና የጉዞ ሂደት ታሪክ ስናነሳ ለቤተ ክርስቲያኒቷ መመስረት እግዚአብሔር ምክንያት ያደረጋቸውን ሃይማኖታዊ ፍቅርና መልካም ራዕይ የነበራቸውን ጥቂት ምዕመናን ማስታወስ ተገቢ ነው ። እግዚአብሔር ሥራውን በሰዎች ላይ አድሮ ይሰራልና ጥቂት ወገኖችን አነሣስቶ በምዕመናን የተመሰረተችው የካንሣስ ደብረ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ወቅቶች ብዙ ውጣ ውረድ የነበረባት ብትሆንም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ በእግዚአብሔር ፈቃድ እዚህ ደረጃ ደርሳ ማየታችን ለእኛ በውስጡ ላለፍን ሁሉ እጅግ አስደሳች በመሆኑ ለዚህ እንድንበቃ የረዳን ቸሩ አምላካችንን እናመሰግነዋለን ።

ከጀማሪዎቹ ምዕመናን መካከል ዛሬም ድረስ በመካከ ላችን የሚገኙ ፤ ወደ ተለያዩ ስቴቶች የሄዱና ወደ ሀገር ቤት ጠቅልለው የገቡ ሲኖሩ ጥቂቶችም የዚህን ዓለም ሩጫ ፈጽመው ወደ ፈጣሪያቸው በሞት ተጠርተዋል ። በህይወት ያሉትን ዕድሜና ጤና እንዲሰጥልን እንዲሁም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩንን ነፍሳቸውን መንግስተ ሰማያትን እንዲያወርስልን እንጸልያለን ።

በካንሣስ ሲቲ አካባቢ እንዲህ እንደ ዛሬው የኢትዮጵያውያን ቁጥር በዝቶ በማይታይበት ወቅት በጊዜው የነበሩት ምእመናን ተሰባስበው በሚወያዩበት ወቅት ወ/ሮ ብዙ ወርቅ ሙሉሰው “ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ እየተሰባሰብን መጽሐፍ ቅዱስ ብንማማር ምን ይመስላትኋል?” በማለት ለወ/ሮ ገነት አሰፋና ለወ/ሮ አሰለፈች መኩሪያ ገለጹላቸው ። እነርሱም በሃሳቡ በመስማማት ቤተ ክርስቲያን ብናገኝና ካህን እያስመጣን ፣ ቅዳሴ እየተቀደሰ ብንሰባሰብ ለእኛም ለልጆቻችንም የበለጠ መልካም ነበር በማለት ሃሳቡን አጠናክረው ሌሎች ምእመናንንም በማወያየት ወደ ተግባር የሚለወጥበትን ሁኔታ አመቻችተዋል።

በመቀጠልም ከመካከላቸው ዶ/ር ዳንኤል ከበደና ወ/ሮ ገነት አሰፋ የተባሉ ምእመናን በኦቨርላንድ ፓርክ አካባቢ የሚገኘው የግሪክ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑትን ካህን ቤተ ክርስቲያናቸውን በወር አንድ ጊዜ ይፈቅዱላቸው ዘንድ ጥያቄ አቀረቡ ። ካህኑም ታህሳሥ 11 ቀን 1988 ዓ.ም. (12/21/1995 እ.ኤ.አ) ፈቃደኝነታቸውን ገለጹላቸው ። ወ/ሮ አሰለፈችም በሴንት ሉዊስ ሚዙሪ ይኖሩ የነበሩትን ቀሲስ አስተርአየ ጽጌን በማነጋገር ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ በመምጣት ለህዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቀዋቸው ፈቃደኛ ሆነው በመምጣታቸው ጥር 5 ቀን 1988 ዓ.ም. (01/14/1996 እ.ኤ.አ) የመጀመሪያው መንፈሳዊ አገልግሎት ተካሄደ ። ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያኗ በቃለ ዓዋዲው መሰረት እንድትተዳደር ለማድረግ በወቅቱ አንዳንድ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ለአሰራር እንዲያመች በማሰብ የሃይማኖት ተቋማት በሚተዳደሩበት ህገ-ደንብ እንድትተዳደር ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጥያቄው ለካንሣስ እስቴት ቀርቦ ታህሣሥ 7 ቀን 1989 ዓ.ም. (12/16/1996 እ.ኤ.አ) ከካንሳስ ስቴት ፈቃድ አግኘታለች ። በወቅቱ መሥራቾች የነበሩትም ወ/ሮ አሰለፈች መኩሪያ ፤ ወ/ሮ ብዙወርቅ ሙሉሰው ፤ ወ/ሮ ገነት አሰፋ፤ዶ/ር ዳንኤል ከበደ፤ አቶ አምዴ ና አቶ አስፋው መላኩ ነበሩ።

ቤተ ክርስቲያኗ በወቅቱ ይዛው ከተነሳችው ዓላማና አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለህዝበ ክርስቲያኑ መስጠት ከሚጠበቅባት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መካከል

  1. በካንሣስና በሚዙሪ አካባቢ ለሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት አምልኮተ
  2. እግዚአብሔርን መፈጸም እንዲችሉ ማድረግ፤
  3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ትምህርት ፤ ትውፊት ፣ ባህልና ታሪክ ማስተማር ፤
  4. ጋብቻን ለሚፈጽሙ ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት እንዲፈጽሙ ማስተማርና አገልግሎቱን መስጠት ፤
  5. ምዕመናን ልጅ ሲወልዱ ሥርዓተ ጥምቀት እንዲፈጸምላቸው ማድረግና ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ጸሎተ ፍትሐት ማድረግ
  6. ከምዕመናኑ መካከል ችግር የገጠማቸው ቢኖሩ እንደ ሁኔታው በሀሣብም በገንዘብም መርዳት የሚሉት ናቸው።

በይበልጥም በግንቦት 15, 1990 ዓ.ም. (05/23/1998 እ.ኤ.አ) ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ከአባ ማርቆስ (አሁን ብፁዕ አቡነ ማርቆስ) ጋር ያደረጉት አባታዊ ቡራኬና ማበረታታት ለቤተ ክርስቲያናችን ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ በማድረጉ በካንሣስና በሚዙሪ አካባቢ የቤተ ክርስቲያንን መቋቋም በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው ሕዝበ ክርስቲያን መሰባሰብ ጀመረ ። ህዝበ ክርስቲያኑ ዕለት በዕለት እየጨመረ በመምጣቱ የራሱ የሆነ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ገዝቶ አምልኮቱን በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት መፈጸም እንዳለበት ስለታመነ እያንዳንዱን ምዕመን በተወሰነ ጊዜ ከፍሎ የሚጨርሰው ገንዘብ ቃል በማስግባትና ፣ በተለያየ ጊዚያትም የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ባደረጉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እስከ አሁን ስንገለገልበት የነበረውን የመጀመሪያውን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ጥር 16, 1994 ዓ.ም. (01/24/2002 እ.ኤ.አ) በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመግዛት ተችሏል ።

በመጨረሻም በየወሩ ከከሴንት ሉዊስ እየመጡ ሲያገለግሉ የነበሩትን ቀሲስ አስተርአየ ጽጌንና በወቅቱ በአካባቢው የነበሩት አባ ቶማስ የተባሉ አባትም በቋሚነት አብረው እንዲያገለግሉ ተጠይቀው ሁለቱም በጥር 2, 1995 ዓ.ም (01/10/2003 እ.ኤ.አ.) ፈቃደኝነታቸውን በመግለጻቸው አገልግሎታቸውን ጀምረዋል። ቤተ ክርስቲያኗም ያልተሟሉ ንዋየተ ቅድሳት እንዲሟሉ ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ በአግባቡ እንዲፈጸምና ደብሩም በብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ደብረ ብርሃን ተብሎ እንዲሰየም አድርገዋል። በተለይም ከተለያዩ እስቴቶች አገልጋይ እንግዶችን በየክብረ በዓሉ እንዲገኙ በመጋበዝና በሚሰጠው አገልግሎትና ትምህርተ ወንጌል ህዝበ ክርስቲያኑ የበለጠ ሃይማኖቱን እንዲያውቅና በማኅበራዊ ህይወቱም እንዲጠናከር አድርጎታል ። ይህ እንቅስቃሴ ህዝበ ክርስቲያኑን በፍቅር አስተሳስሮት ቤተ ክርስቲያኗ በሰላምና በአንድነት እየተመራች ነበር ።

ይሁንና ሳይታሰብ በድንገት በተነሣው የነገረ ሃይማኖት ውዝግብ ምክንያት በምእመናኑ መካከል ያልተጠበቀና ፈታኝ የሆነ ችግር ስለተከሰተ በወቅቱ የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት (የዛሬው ብፁዕ ወቅዱስ) አቡነ ማትያስ ከኒውዮርክ በመምጣት ጉዳዩን ተመልክተውት የመጨረሻ ሃይማኖታዊ ውሳኔ በማሳለፋቸው ችግሩ እልባት ሊያገኝ ችሏል ። ህዝበ ክርስቲያኑም የበለጠ ተጠናክረው ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጡትን ፈተናዎች በመቋቋም ከቀሩት አገልጋዮችና ወጣት መዘምራን ጋር በመሆን ካህን ሲገኝ በጸሎተ ቅዳሴ ፤ ካህን ሲጠፋም በትምህርተ ወንጌል ፣ በዝማሬና በምህላ አሳልፈዋል።

ምእመናኑም አገልጋይ (ካህን) ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው ከረጅም ጊዜ ፍለጋ በኋላ ቦስተን አካባቢ የነበሩ መልአከ ጽዮን አባ ህሩይ መሸሻ የተባሉ አባት በማግኝታቸውና እሳቸውም መጥተው በቋሚነት ለማገልገል በመስማማታቸው የምዕመናኑ ተስፋ እንደገና ለመለመ ፤ ተስፋ ቆርጦ በየቤቱ ተቀምጦ የነበረው ምዕመንም ተመልሶ መምጣት ጀመረ ። ይህ ወቅትም የተለያዩ መምህራንን በመጋበዝ የወንጌል ትምህርት በሰፊው መሰጠት የተጀመረበት ፣ በመቀያየምና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተ ክርስቲያን ቀርተው የነበሩ ምዕመናንን የእርቅ ኮሚቴን በማዋቀር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ ጥረት የተደረገበት ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ፣ የኒውዮርክና የአካባቢዋ ሀገረ ስብከት ሥር እንድድትተዳደር የተደረገበት ነበር ።

በመጨረሻም የነበሩት ካህን ወደ ሌላ ቦታ በዛወራቸው ሰበካ ጉባዔው ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሐም ጋር ከተመካከረ በኋላ በቋሚነት የሚያገለግሉት ካህን እስኪመጡ ድረስ ቀሲስ ተክለ ማርያም የተባሉ ካህን በጊዜያዊነት እንዲያገለግሉ በብፁዕነታቸው ተመድበው ለሶስት ወራት ያህል ሲያገለግሉ ቆይተዋል ።

በመጨረሻም አሁን በአገልግሎት ላይ የሚገኙት መልአከ ሰላም አባ ተስፋ ማርያም መርሻ በብፁዕ አቡነ አብርሐም በአስተዳዳሪነት ተመድበዋል ። እኒህ አባት ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን የአገልግሎት ዘርፍ በማጠናከርና የምዕመናኑን መንፈሳዊ ሕይወት በጥሩ ሁኔታ በማጠናከር ፣ የትምህርተ ሃይማኖት ኮርስ በጥልቀት ለተከታታይ ጊዜያት በማስተማርና በማስመረቅ ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ፣ ለምሳሌ የማህሌተ ጽጌን አገልግሎት በመስጠት ፣ በየክብረ በዓላትም ዋዜማና የተሟላ የማህሌት አገልግሎት በመስጠት ፣ የተለያዩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በተደጋጋሚ በመጋበዝ ለህዝበ ክርስቲያኑ ትምሕርተ ወንጌልን በማዳረስ ፣ ምዕመናንን በቅርበት በማስተማርና በመምከር ንስሐ እንዲገቡና ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ እንዲበቁ በማድረግ ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቱንም ከመዝሙር ባለፈ በሥነ-ጽሁፍና በህጻናት ክፍል እንዲደራጅ በማድረግና የትምህርት ንዑስ ክፍልም እንዲቋቋም በማድረግ ብርቱ ጥረት ተደርጓል ።

በዚህ ወቅት የተመረጠው አዲስ የሰበካ ጉባዔ በልማት ረገድ ዕቅድና ፕሮግራም በመንደፍ ፣ ሁሉንም ምእመናን በአገልጎልት በማሳተፍና የበረከት ተካፋይ እንዲሆኑ ፣ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለሁሉም እንዲዳረስ ለማድረግ እንዲቻል በማሰብ የተለያዩ ንዑሳን ክፍሎችን አቋቁሞ ምእመናኑ በኮሚቴነት እየገቡ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል ። በይበልጥም በምዕመናን መካከል ሊኖር የሚችለውን መንፈሳዊና ቤተሰባዊ ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በየሦስት ወሩ የሚቀያየሩና ከሰበካ ጉባዔው አንድ ተወካይ ጋር ከምእመናን ሦስት አባላት ያሉበት የእለተ ሰንበትና የከብረ በዓላት አስተናጋጆችን በመመደብ የተዘረጋው አሰራር ብዙ ምእመናንን ከማሳተፉም ባለፈ ከሚጠበቀው በላይ መልካም ውጤት አስገኝቷል ።

እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗ አባላት የአባልነት ቅፅ እንዲሞሉና የወርሃዊ የአባላት መዋጮን ከባንካቸው በቀጥታ ክፍያ እንዲከፍሉ በተደረጉ እንቅስቃሴዎችና ምዕመናኑም ባሳዩት ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ የአባላቱ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን መብዛትና የቤተ ክርስቲያኒቷ የገንዘብ አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ዕዳ ተከፍሎ አልቆ በጣይነት ቤተ ክርስቲያኗ ለምታቅደው የልማት ሥራ አቅም እንዲፈጥር አስችሏል ። በመጨረሻም የቅዱስ ሚካኤል ጽላት በብፁዕ አቡነ አብርሐም ተባርኮ እንዲገባ ተደርጎ ቅዳሴ ቤቱ እንዲከበር ተደርጓል ። ሰበካ ጉባዔውም የሁለት ዓመታት ቆይታውን ስላጠናቀቀ በምእመናን አዲስ የሰበካ ጉባዔ አስመርጦ ሃላፊነቱን አስረክቧል።


አዲስ የተመረጠው ሰበካ ጉባዔም የተጀመሩ ሥራዎችን ከማጠናከር በተጨማሪ ቀደም ሲል አንድ የነበረውን የልማትና የህንጻ ኮሚቴ የሥራውን ስፋት በማየትና ተጨማሪ ምእመናንም እንዲሳተፉ በማሰብ የህንፃና የልማት ክፍልን ራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ በማስቻል ሌሎችንም ክፍሎች የበለጠ እንዲጠናከሩ አድርጓል ። ከዚህ ጎን ለጎንም በምእመናን ብዛት የሚፈጠረውን የቦታ ጥበት ለማስቀረት ፣ ልጆችንም በየዕድሜያቸው ከፋፍሎ በተለያዩ ክፍሎች ለማስተማርና በይበልጥም በሌሊት በሚካሄደዉ የማህሌት አገልግሎት ጊዜ የአካባቢ ጎረቤቶች መረበሻቸውን በተደጋጋሚ ስላሳሰቡን ከምንጊዜዉም በላይ ሌላ ህንጻ ማስፍለጉን ከህንጻ ኮሚቴው ጋር በስፋት በመመካከርና ጉዳዩንም ለምእመናንን አቅርቦ በማጸደቅ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ዛሬ የምናየው ሰፊ ቦታ ሚያዝያ 23, 2005 (May 1 2013) እንዲገዛ አድርጓል ።

ቤተ ክርስቲያኗ ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ከሚያበረክቱት አገልግሎት ጋር በመንፈሳዊዉም ሆነ በልማቱ ዘርፍ በመደበኛና በበጎ ፈቃደኝንት አገልግሎት የሚሰጡ ካህናት ለተገኘው ውጤት ዓይነተኛ ተጠቃሾች ሲሆኑ ፤ በተለይ ያላቸውን የዕረፍት ጊዜ እያብቃቁ ሳይሰለቹና ተስፋ ሳይቆርጡ ሰፊ አገልግሎት የሚሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ዲያቆናትን ለሰጠንና ከትንሽ አንስቶ ቤተ መቅደሳችን በአገልጋዮች እስኪሞላ ድረስ በበረከት ለጎበኘን አምላክ ክብርና ምስጋና እናቀርባለን ።

በመቀጠልም ሰበካ ጉባዔው የተዘረጋውን ሰፊ አገልግሎት በአንድ ካህን ብቻ ለማስቀጠል አስቸጋሪ ስለሆነ ተጨማሪ ካህን እንደሚያስፈልግ ወስኖ ዛሬ ከእኛ ጋር የምታዩአቸውን በቤተ ክርስቲያን ዕውቀት የተካኑ ሁለ ገብ ሙያ ያላቸውን ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም ምሕረቱን ከኢትዮጵያ በማስመጣት አገልግሎቱ የበለጠ እንዲጠናከር አድርጓል።

ቤተ ክርስቲያን በእለተ ዐርብ በቀራንዮ አደባባይ ባፈሰሰው በገዛ ደሙ የዋጃትና የፀጋው ግምጃ ቤት ያደረጋት እንደመሆኗ መጠን እግዚአብሔር አምላክ በበረከቱ እየጎበኛት ልጆቹ ምእመናንን የሚባርክበት የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለህዝበ ክርስቲያኑ ስትሰጥ ቆይታለች ። ይኸውም በርካታ ህጻናትን በዓርባና በሰማንያ ቀናቸው እያጠመቀች የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ አድርጋለች ። በርካታ ወጣቶችንም በምክረ ካህን እንዲኖሩና ጋብቻቸውንም በሥርዓተ ተክሊልና በቅዱስ ቁርባን እንዲፈፅሙ አድርጋለች ። ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ምዕመናንም ጸሎተ ፍትሐት በመፈፀም በክብር እንዲሸኙ አድርጋለች ። በተጨማሪም ከአጎራባች አብያተ ክርስቲያናት ጋር መልካም ግንኙነት ከመፍጠር ባሻገር ሌሎች ቋሚ አገልጋይ የሌላቸውን አዳዲስ ተቋቋሚ ማኅበረ ምዕመናንም ካሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ የማስተማርና የማደራጀት አግለገሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች ፤ ወደፊትም ይህንኑ ተግባሯን አጠናክራ ትቀጥልበታለች።

ለእናቱ የምሕረት ቃል ኪዳን በሰጠበት (ኪዳነ ምህረት) ስም አሰባስቦ አገልግሎታችንን ያስጀመረን ፣ በጉዟችን ሁሉ ያልተለየን ፤ በመከራችንና በችግራችን ጊዜ ረድኤቱን ከእኛ ያላራቀ ፣ በድካማችን ሁሉ አበርትቶ ለዚህ እድገትና ክብር ያበቃን ቸሩ አምላካችን ክብርም ምስጋም ለዘለዓለሙ ለርሱ ይሁን አሜን ።