ሃይማኖት ፤ ሃይመነ አሳመነ ፡ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ፤ ትርጉሙም በአንድ አምላክ ማመን ለአንድ አምላክ መታመን ማለትን ይገልጻል ።
“ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠሩ የሚታየውም ከማይታየው እንደሆነ እናውቃለን። ዕብራውያን 11፥ 3
በዓይናችን ለምናየው ለግዙፉ ዓለምና ለማይታየው ለረቂቁ ዓለም ፈጠሪ አስገኝ መጋቢ አለው ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው ብሎ ማመን የሃይማኖት መጀመሪያ ነው።
የሃይማኖት ትምሕርት፤ የሚነገረው የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን በመቀበል የምናምነውን የምንማርበት እንጅ ፣ እንደ ሳይንሳዊ ዕውቀት የተማርነውን ሁሉ በዘመናዊ መሳሪያ አረጋግጠን የምንደርስበት ስላልሆነ ፤ አስቀድመን በህሊናችን በመመራት የእግዚአብሔርን መኖር ማመን ተገቢ ነው ። ሃይማኖት ቁስ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ታምነው የሚኖሩት ሕይወት ነውና ። አይጠቀሙበትም እንጅ “አጋንንትም ሳይቀሩ የአምላክን መኖር ያምናሉ ይንቀጠቀጣሉም ። ያዕቆ 2 ፥ 19 ። በዚህ ዓለም በራሱ የተገኘ ምንም ነገር እንደሌለና ለሁሉም አስገኝ እንዳለው ይታወቃል ። ይሁን እንጂ በሃይማኖት ካልሆነ በቀር ሁሉን የፈጠረውን አምላክ የሳይንስ የምርምር ውጤት በሆነው የሥጋዊ ጥበብ ተመራምሮ አይደረሰበትም ። በሃይማኖት ትምሕርት ግን ሁሉን ያስገኘ እግዚአብሔር መሆኑን እናውቃለን ። የሰው ልጅ የሠራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚያንቀሳቅስ ባለሞያ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ይህን ዓለምም የሚያንቀሳቅሰውና የሚመራው ፤ አስገኚው (የፈጠረው) አምላክ ብቻ ነው ። ሰው ይህን የአምላክ ሥራ
አይቶ ፈጣሪውን ማመስገን ሲገባው ሁሉንም ነገር የተፈጥሮ ክስተት ነው ሲል ይደመጣል
ለምሳሌ ጨለማና ብርሃንን ፣ ወቅቶችንና ዘመናትን ፣ የሚያፈራርቅ ፤ የሰውን ልደትና ሞት የሚወስን ፤ ፍጥረታት ሁሉ ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የሚያደርግ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠራቸው አምላክ ብቻ ነው ፤ የሰው ልጅ የተደረጉና ያለፉ ታሪኮችን ከመመዝገብ ያለፈ ችሎታ የለውም ።
እምነት ፤ ማለትም ፡ አምነ አመነ ፣ ካለውየግዕዝ ቃልየተገኘ ሆኖ ትርጉሙም ሃይማኖት ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው ። ቅዱስ ጳውሎስ
“በሥጋ ዓይን የማናየውንና ተስፋ የምናደርገውን የሚያስረዳና የሚያስረግጥ መሳሪያ ነው” በዕብ 11፥1
በማለት እንዳስተማረን ፤ በሃይማኖት የሚኖር ሰው ዕለት ዕለት በሚያደርግለት የቸርነት ሥራው አምላኩን ያየዋል ለማያምንና ፍጥረታዊ ለሆነ ሰው ግን የሃይማኖት ነገርለእሱ ሞኝነት ስለሆነ ለህሊናው ሊረዳውና ሊቀበለው አይችልም።(1ቆሮ ፡ 2 ፥ 9)
ሃይማኖት ፤ መንታነት የሌለባት ፡ ከቅዱሳን መላእክት ጀምሮ ሰዎችና እግዚአብሔር የሚገናኙባት አንዲት መንገድ ናት። (ኤፌሶን ፡ 4 ፥ 4)
ይህም –
- ቅዱሳን መላእክት ፤ ሰይጣን ዲያብሎስ “ፈጣሪ ነኝ” ባለበት ወቅት ፤ ቅዱስ ገብርኤል “አምላካችን እስኪገለጥልን ድረስ በእምነታችን እንጽና” ብሎ የተናገረውን ቃል ፤ መሪ በማድረግ በሃይማኖት ጸንተው ተገኝተዋል። (ራዕየ ዮሐንስ 12 ፥ 7)
- ከአዳም እስከ ሙሴ ፤ የነበሩት የተጻፈ ህግ ሳይኖራቸው በህገ ልቡና እየተመሩ በሃይማኖት ጸንተው ኖረዋል
- ከሙሴ እስከ ክርስቶስ ፤ የነበሩ ቅዱሳን ሰዎች ፤ ቃሉን ሰምተው በመጠበቅ በሃይማኖታቸው ተመስክሮላቸው አልፈዋል ። ዕብራውን ፡ 11 ፡ 4 ።
- ሐዋርያት ፤ ቃሉን ሰምተው ፣ ተአምራቱን አይተው ፣ ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ለሌላውም አስተምረው ክርስትናን በዓለም አስፋፍተው በክብር አልፈዋል ።
- ከሐዋርያት በኋላ የነበሩት ሁሉ ፤ ከቅዱሳት መጻህፍትና ከቅዱሳን ሕይወት ተረድተው ፣ ከመምህራን እየተማሩና በየዘመናቱ የሚደረገውን ተአምራት እያዩ ፤ በሃይማኖት ጸንተው ኖረዋል ፣ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚቀጥሉ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ይኖራሉም ። ስለሆነም የሃይማኖት ጉዞ በአምላክ ፈቃድ የሆነና በዘመናት ሁሉ የነበረ ያለና የሚኖር ሂደት ነው ።
ሃይማኖት ፤ የማታረጅ ፣ የማትታደስ ፣ በየዘመኑ በሚነሳ ሥልጣኔ የማትለወጥ ሁሌም አዲስ ናት። ሃይማኖት ፤ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ሆነው ፡ ምሥጋና በማቅረብ ክብሩን ወርሰው እንዲኖሩ የሚያስችልና በልብ አምኖ በአንደበት መስክሮ የሚዳንበትየተቀደሰ ሕይወት ነው። (ሮሜ ፡ 10፥10)
ከዚህ ከተቀደሰና ከትትክለኛው መንገድ የወጡ ሰዎች በዘመናችን እንደምንሰማው ፡ ከመጠራጠር ተነስተው እኛ ትንንሽ ከርስቶሶች ነን እስከ ማለት ደርሰዋል ። የሰው ልጅ ለህሊናው ገደብ ካላበጀለትና ለእግዚአብሔር ክብር መስጠትን ከረሳ ፡ መጨረሻው ጥፋት መሆኑን ከዚሀ መረዳት እንችላለን ።
ሃይማኖታችን በምግባር የሚገለጥ መሆን አለበት ። በሥራ የማይገለጥ ሃይማኖት ፡ ነፍስ የተለየችው ሥጋ “በድን” ማለት ነውና። ያዕቆብ 2 ፥ 26 ።
Leave A Comment