1. የክርስቲያኖች  ስደት በሳውል ቅንዓት [ሐዋ 8፡32]
 2. የሳውል ወደ ክርስትና መጠራት [ሐዋ 9፡5]
 3. ካሕኑ ሐናንያ ሳውልን ማጥመቁ  [ሐዋ 9፡17]
 4. በአይሁድ ተቃውሞ በቅርጫት መጣሉ  [ሐዋ 9፡25]
 5. ጠንቅዋዩ በርያሱስን አይኑን ማሳወሩ [ሐዋ 13፡26]
 6. ስብከቱ ያመነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ስሙን ለጳውሎስ መስጠቱ   [ሐዋ 13፡13]
 7. ከጠንቅዋይዋ ሴት ርኩስ  መንፈስ ማስወጣቱ  [ሐዋ 16፡16]
 8. ጳውሎስና ሲላስ በእስር ቤት ሕይወት [ሐዋ 16፡22 ]
 9. በአቴና ቤተ ጣዖት(አርዮስፋጎስ) መስበኩ [ሐዋ 17]
 10. በ3 ነገስታት ፊልክስ፡ፊስጦስ ፡አግሪጳ ፊት ለፍርድ መቅረቡ  [ሐዋ 24፡2 -26፡1-28]
 11. መልእክታቱ ለሀገርና ለግለሰብ የተላኩ ሲሆን
 • ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ከ46-60 ዓ\ም  ተልከዋል
 • ለፊልሞና የተላከ መልእክት በ60 ዓ\ም
 • ለቲቶ የተላከ መልእክት በ63 ዓ\ም
 • ለጢሞቴዎስ የተላከ መልእክት በ66ዓ\ም

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን መልእክት ልኮ አንድ ዓመት ከ3ወር ቆዪቶ በሰማዕትነት አርፎአል የሐዋርያው  ቅ/ጳውሎስ በረከት ይደርብን አሜን።

 1. ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያሳድድ ነበር። ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ  ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር።
 2. ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?
 • ጌታ ሆይ አንተ ማን ነህ?
 • አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። የመውጊያውን ብረት ብትቃወም አንተ ይብስብሃል።
 • ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?
 • ተነስተህ ወደከተማ ግባ እና ታደርገው ዘንድ የሚገባህን ይነግሩሃል።  [ሐዋ 9 : 5]
 1. ጌታም በራዕይ  
  • ሐናንያ ሆይ?
  • ጌታ ሆይ እነሆኝ አለሁ
  • ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤  እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል አለው።
  • ሐናንያም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤  በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ።
  • ጌታም። ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።
  •  ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ። ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ።  [ሐዋ 9 : 10-19]
 2. በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤  ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት። [ሐዋ 9 : 23-25]
 3. እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ ፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው። አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። [ሐዋ 13 : 8-12]
 4.  በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አምኖ ተጠመቀ። ስሙንም ለሳውል ለቀቀለት ፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጳውሎስ ተብሎ ተጠራ። [ሐዋ 13:12-14]
 5. የምዋርት መንፈስ ያደረባት ጠንቋይ ሴት በሕዝቡ መካከል እነ ቅዱስ ጳውሎስ እየተከተለች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባርያዎች ናቸው።

ጳውሎስ ዘወር ብሎ አያትና መንፈሱን ከእሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለው አለው። በዚያም ሰዓት ወጣ። [ሐዋ 16 : 16-18]

 1. ጳውሎስ እና ሲላስ በእስር ቤት እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ሲያመሰግኑ(መዝሙር) እስረኞች ያደምጡ የወህኒውም መሰረት ይናወጥ  ነበር። (ወዘተ) ዘበኛው ወደቤቱ ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው ከቤተሰቦቹ ጋርም አምኖ ተጠመቀ። [ሐዋ 16:24 – 34]
 2. ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ። የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።  ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤  እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።  ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።  እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። [ ሐዋ 17 : 22-31]
 3. በሦስቱ ነገስታት (ፊልክስ ፤ ፊስጦስ ፤ አግሪጳ) ፊት ለፍርድ መቅረቡ

ጳውሎስ በሃገረ ገዠው ፊልክስ ፊት

ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል። ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤

እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ።

ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም።

አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም።

ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤

እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።

ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።

ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤

ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ።

ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ።

ወይም በመካከላቸው ቆሜ። ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዓመፃ ያገኙ እንደ ሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ።

ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና። የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው።

የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው።

ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው።

እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ። አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።

ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር።

ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው። [ሐዋ 24:10-ፍም]

ጳውሎስ በፊሲጦስ ፊት

ጳውሎስም ሲምዋገት። የአይሁድን ህግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሳርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም አለ።

ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን። ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር ከዚያው በፊቴ ትፋረድ ዘንድ ትወዳለህን? ብሎ መለሰለት።

ጳውሎስ ግን። እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልሁም።

እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደ ሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብዬአለሁ አለ።

በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብለሃል፤ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ ብሎ መለሰለት።

ከጥቂት ቀንም በኋላ ንጉሡ አግሪጳ በርኒቄም ለፊስጦስ ሰላምታ እንዲያቀርቡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ።

በዚያውም ብዙ ቀን ስለተቀመጡ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ገለጠ። ፊልክስ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ፤

በኢየሩሳሌምም ሳለሁ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እፈርድበት ዘንድ እየለመኑ ስለ እርሱ አመለከቱኝ።

እኔም። ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው።

ስለዚህም በዚህ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ሳልዘገይ በማግሥቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ያንን ሰው ያመጡት ዘንድ አዘዝሁ።

ከሳሾቹም በቆሙ ጊዜ እኔ ያሰብሁትን ክፉ ነገር ክስ ምንም አላመጡበትም፤

ነገር ግን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ጳውሎስ። ሕያው ነው ስለሚለው ስለ ሞተው ኢየሱስ ስለ ተባለው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር።

እኔም ይህን ነገር እንዴት እንድመረምር አመንትቼ። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚህ ነገር ከዚያ ልትፋረድ ትወዳለህን? አልሁት።

ጳውሎስ ግን አውግስጦስ ቄሣር እስኪቈርጥ ድረስ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ ይጠበቅ ዘንድ አዘዝሁ።

አግሪጳም ፊስጦስን። ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር አለው። እርሱም። ነገ ትሰማዋለህ አለው።

በነገውም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስን አመጡት።

ፊስጦስም አለ። አግሪጳ ንጉሥ ሆይ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ።

እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፥ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቈረጥሁ።

ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም በፊትህ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አመጣሁት፤

እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና። [ሐዋ 25 : 8-27]

ጳውሎስ በንጉስ አግሪጳ ፊት

አግሪጳም ጳውሎስን። ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ መለሰ እንዲህ ሲል።

ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤

ሊመሰክሩ ይወዱ እንደ ሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና።

አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ።

ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ።

እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል?

እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር።

ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ።

በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቈጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር።

ስለዚህም ነገ ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥

ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤

ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ።

እኔም። ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።

ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና።

የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።

ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም።

ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ።

ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ።

ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም።

እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ። ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል አለው።

ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ። ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአእምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም።

በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና።

ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ።

አግሪጳም ጳውሎስን። በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ አለው።

ጳውሎስም። በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራቴ በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ አለው።

ንጉሡም አገረ ገዡም በርኒቄም ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፥

ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ ብለው ተነጋገሩ። [ሐዋ 26 : 1-31]

 1. ለአህጉር  እና ለግለሰቦች የተጻፉ 14  መልዕክቶች
 • ለአህጉር ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ከ46-60 ዓ\ም ተጽፈው  ተልከዋል
 • ለግለሰብ
 1. ለፊልሞና የተላከ መልእክት በ60 ዓ\ም
 2. ለቲቶ የተላከ መልእክት በ63 ዓ\ም
 3. ለጢሞቴዎስ የተላከ መልእክት በ66ዓ\ም

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን መልእክት ልኮ አንድ ዓመት 3ወር ቆዪቶ በሰማዕትነት አርፎአል የሐዋርያው  /ጳውሎስ በረከት ይደርብን አሜን።