ይህ ቃል ፣ ሐዋርያት አይሑድን ፈርተው በተዘጋ ቤት ውስጥ እያሉ ፡ ጌታችን በሩ እንደተዘጋ ገብቶ በመካከላቸው ቆሞ የተናገረው የምስራችና የማጽናኛ ቃል ነው ።

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸውና መንፈሳዊ ኃይል ከማግኘታቸው በፊት እንደማንኛውም ሰው በሥጋቸው ይፈሩ ስለነበረ ጌታችን ከተያዘበት ጸሎተ ሐሙስ ማታ ጀምሮ ተበታትነው ነበር ። በተለይ ቅዱስ ጴጥሮስ “ምንም ቢመጣ ከአንተ አልለይም” እያለ ሲምል ሲገዘት እንዳልነበረ ሁሉ ፡ ጌታችን “ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ” እንዳለው “አላውቀውም” ብሎ እስከ መካድ ደርሶ ነበር ። እርግጥ ነው ወዲያውኑ ተጸጽቶ በንስሐ ዕንባ ተመልሷል ። ማርቆስ 14 ፡ 27-72 ። የሰው ልጅ በሃይማኖት ካልጠነከረ በቀር መከራ በደረሰበት ጊዜ ወይም በጊዜዊ ጥቅም ተታሎ ፈጥኖ ሊክድ ይችላል ። ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ወርቅነቱ እንደሚታወቅ ሁሉ ሃይማኖታችንም የሚለካውበመከራጊዜጸንቶበማለፍነው። ማቴ24።13።

አይሑድ ጌታችን እንደሚነሳ አስቀድመው ቢሰሙም እውነትነቱን ባለማመናቸው ምክንያት በመቃበሩ ዙሪያ ብዙ ጠባቂዎችን አሰማርተው ያስጠብቁ ነበር ። ጌታችን ግን “ጠላቶቹን ወደኋላው አስወግዶ…” መዝ 78 ፡ 66 ። ከተነሳ በኋላ ጠባቂዎቹ በሆነው ነገር ተደናግጠው ሸሽተዋል ። እርግጥ ነው አይሑድ ሊያምኑ ቢፈልጉ ኖሮ ገና ማስተማር ከመጀመሩ በፊት በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የተደረውን ታምራት አይተው ባመኑ ፡ የዮሐንስንም ምክርነት ሰምተው በተከተሉት ነበር ። ማቴ 3 ፡ 11-17 ። ዮሐንስ 1 ፡ 19-37 ። በጠባቂነት ቀጥረው ያስቀመጧቸው ወታደሮች ለአይሑድ ፡ የጌታችንን ትንሳኤ በነገሯቸው ጊዜም በተለመደው እልኸኝነታቸው በመግፋት እውነቱን በገንዘብ ኃይል አድበስብሰው ለማስቀረት ሞከሩ እንጅ ተጸጽተው የመመለስ ቅንጣት ምልክት አላሳዩም ። ማቴ 28 ፡ 11-15 ።

ጌታችን ከተነሳ በኋላ በመጀመሪያ ለማርያም መግደላዊት በመቃብሩ ቦታ ተገለጠላት ፡ ዮሐንስ 20 ፡ 15 -17 ። ቀጥሎም ሐዋርያት አይሑድን ፈርተው በዝግ ቤት ውስጥ እያሉ ቤቱን ሳይከፍት እንደተዘጋ ገብቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው ። ሐዋርያትም በደስታ ትንሳኤውን አመኑ ። እኛ ክርስቲያኖችም በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጸናልና የጌታን ትንሳኤ አምነን ለዓለም እንመሰክራለን ። ኤፌሶን 2 ፡ 20 ። የጌታችንን ትንሳኤ የሚያምኑ ሁሉ የሰው ልጆች ሁሉ (ጻድቃን የክብር ፣ ኃጥዓን የፍርድ ትንሳኤ) እንደሚነሱ አምነው በተስፋ ይጠብቃሉ ። ዮሐንስ 5 ፡ 28 -29 ።

ጌታችን ሐዋርያትን ያጽናናበት ቃል “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ ነው ። ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው ። የሰው ልጅ እውነተኛ ሰላም ከሌለው ሁሉ ነገሩ ይታወካል ። እውነኛ ሰላም የሚባለውም ፡ ከሌሎች የምናገኛውን ነገሮች ምክንያት ያላደረገ ሲሆን ነው ። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን በከባድ ቅጣትና ማስጠንቀቂያ ወይም ጥቅማቸውን በማስቀረት ፤ ጸጥ እንዲሉ በማድረግ በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉ መስሎ ይሰማቸው ይሆናል ። ሌሎች ጉልበትና አቅም ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ባለሥልጣኖች ወይም ብዙ መሳሪያ ያላቸው ሀብታም አገሮችም (መንግሥታት) አቅም የሌላቸውን ሰዎችና አገሮች (መንግሥታት) በኃይል በማንበርከክ ለጊዜው ጸጥ እንዲሉ ሊያደርጓቸው ይሞክሩ ይሆናል ። ይህ ግን ዘላቂ ሰላም ሊሆን አይችልም ፤ ምክንያቱም በኃይል ዝም ያለ የኃይል ሚዛኑ ሲለወጥ ፤ በጥቅሙ ምክንያት ለጊዜው ጸጥ ያለ የመሰለውም የለመደው ጥቅሙ ሲጓደልበት ፣ ሰላሙ መቋረጡ አይቀርምና ነው ።

ክርስቶስ የሰጠንን እውነተኛ ሰላም የሚያውቁትና የሚኖሩበት ግን የእግዚአብሔርን ቃል የሚያውቁና እንደ ቃሉ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ናቸው ። ጌታችን “እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም” ብሎ እንዳስተማረን ፤ እንደ ዓለማውያን አስተሳሰብ ይህን ሰላም መረዳት ግን አይቻልም ። ዮሐንስ 14 ፡ 27 ።

በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ከውጭ በሚመጣ ምክንያት ላይ የተንጠለጠለና ተለዋዋጭነት ያለውን የዓለም ሰላም ሳይሆን ፡ ክርስቶስ የተወልንን እውነተኛ ሰላም በዕለት ተለት ሕይወታችን ውስጥ ልንለማመደው ይገባናል ። የክርስርቶስ ሰላም ከሌላው ምንም ሳይጠብቁ የራስን በልግስና መስጠት ፤ ከራስ ይልቅ ለሌላው መኖር ማለት ነው ። ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ የክርስቶስ ልብ አለን” ብሎ እንዳስተማረን ፤ 1 ቆሮንቶስ 2 ፡ 16 ። በእውነተኛ የክርስቶስ መንገድ ካልኖርን በቀር እንደ ዓለማውያን ፍልስፍና ይህን ልንረዳው አንችልም ። ስለዚህ እኛነታችንን ለክርስቶስ ሰላም እንደሚመች አድርገን መለወጥ አለብን እንጅ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ እኛ የማይረካ ፍላጎት ለማስተካከል የምናደርገውን ልምምድ ዛሬውኑ ለማቆም መወሰን አለብን ። እኛ አኮ ምንም ቢሰጠን መርካትን የማንችልና የፍላጎታችንን ጣራ መረዳት የማንችል ስግብግቦች ነን ። ልንረካ የምንችለውና ኑሮዬ ይበቃኛል ልንል የምንችለው ፣ እንደ ቃሉ መኖር ስንጀምር ብቻ ነው ። 1 ጢሞቴዎስ 6 ፡ 6 ።

ሐዋርያትም ጌታችን “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ ሰላሙን ከሰጣቸው በኋላ ፤ መውደቅ መነሳት ፣ ከበዛት የፍርሃት አስተሳሰባቸው ተላቀውና መከራንና ሰደትን በደስታ ተቀብለው ለሌሎች ብርሃን ሆነው አልፈዋል ። የሐዋርያት ሥራ 5 ፡ 41 ። በሐዋርያት መሠረት ላይ መታነጽ ማለት ይህ ነው ። ክርስትና የሚጠሩበት ስም ሳይሆን ፡ የሚኖሩትና ለሌላውም በግልጽ የሚመሰክሩት ሕይወት ነውና ።

ከመልአከ ሰላም አባ ተስፋ ማርያም ላቀ