ካህን ፦ ተክህነ አገለገለ ። ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ፤ ካህን ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ፤ የምዕመናን አባት ፤ ጠባቂ ፤ መጋቢ ማለት ነው ።

ምሥጢረ ክህነት በብሉይ ኪዳን

የክህነት አንዱ መገለጫው መስዋዕት ማቅረብ ሲሆን ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ አገልግሎት የተመረጠውና ካህን ተብሎ የተጠራው መልከ ጼዴቅ ነው ። ዘፍ 14፥18 ። በኋላም እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የሕዝቡን ኃጢአት እየተቀበለ ከእግዚአብሔር የሚያስታርቅ ካህን እንዲመርጥ ሙሴን ስላዘዘው ከመልከ ጼዴቅ በኋላ አሮን ተሾመ ።

ከአሮን እስከ ዮሐንስ መጥምቅ ደረስ ረጅሙን የብሉይ ኪዳን ዘመን ከአሮን ዘር ብቻ የሚወለዱት ቅብዓ ክህነት እየተቀቡ በካህንነት እያገለገሉ አልፈዋል ።

ነገር ግን በዘር ሐረግ ላይ የተመሠረተው ክህነት ለሐዲስ ኪዳኑ ክህነት ምሳሌ ስለነበረ ፍፁምና ዘላቂ አልነበረምና መስዋዕቱም ሆነ የአመራረጡ ሂደት በሌላ ተተካ ።

ዘላቂ ያልሆነበትና በሌላ የተተካበት ምክንያት

  • ክህነቱ በዘር ብቻ የተገደበ ስለነበረ በሐዲስ ኪዳን ህጉንና ሥርዓቱን አሟልቶ ለተገኘ ለማንኛውም ሕዝብ የተፈቀደ ሆነ ። ክርስቶስ የመጣው ለዓለም ሁሉ ነውና ።
  • መስዋዕታቸው ፍጹም ድኅነት የማያሰጥ በመሆኑ በክርስቶስ ሥጋና ደም ተተካ ። ዮሐ 6 ፥ 32 ።
  • አገልግሎቱ ለጊዜው ከሥጋ መቅሰፍት ከማዳን ያላለፈ ነበረ ፤ በሐዲስ ኪዳን ግን በምድርም በሰማይም ማሰር በሚችሉ ፣ በነፍስም በስጋም ላይ ሥልጣን ባላቸው ካህናት ተተካ ። ማቴ 18 ፥ 18 ።

ምሥጢረ ክህነት በሐዲስ ኪዳን

በብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ካህን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሲሆን ፤ ከእሱ በኋላ የብሉይ ኪዳን ክህነት አልፏል ። ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ፡ ካህኑ በሚገኝበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ሄደን በካህኑ እጅ መጠመቅ እንዳለብን አስተምሮናል ። ማቴ 3 ፥13 ።

ጌታችን ሲያስተምር ስለ ካህናት በብዙ ቦታ ተናግሯል ። ሂድና ራስህን ለካህን አሳይ ። ማቴ 8 ፥ 4 ። አንተ ብፁዕ ነህ ፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻ እሰጥሃለሁ… ። ማቴ 16 ፥ 17 ። እውነት እላችኋለሁ በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ፣ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል ። ማቴ 18 ፥ 18 ። ይህን የተናገረው በመዋዕለ ስብከቱ ሲሆን ከሙታን ከተነሳ በኋላም ለሐዋርያት አረጋግጦላቸዋል ። ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ። ማቴ 28 ፥ 19 ።..እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ። ዮሐ 20 ፥ 22 ። በመጨረሻም ቅዱስ ዼጥሮስን “….ስምዖን ሆይ በጎቼን ጠብቅ ፤ (ለጊዜው አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ፡ ለፍጻሜው ወላጆችን) ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ ፤ (ለጊዜው ሰብዓ አርድዕትን ፡ ለፍጻሜው ወጣቶችን) ፣ ግልገሎቼን ጠብቅ (ለጊዜው ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስትን ፡ ለፍጻሜው ህጻናትን)” በማለት ሐዋርያትን ዸዸሳት ፣ ቅዱስ ዼጥሮስን የመጀመሪያ ሊቀ ዻዻሳት አድርጎ ሾመው ። ዮሐ 21 ፥ 15 ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ዸዸስና በዸዸሳት በሚመራ መንፈሳዊ ጉባኤ (ቅዱስ ሲኖዶስ) አማካኝነት እየተመራች አገልግሎቷን ታካሂዳለች ።

የክህነት ደረጃዎች

ሊቀ ዻሳሳት

ሊቃነ ዸሳሳት “ፓትርያርክ” እየተባለም ይጠራል ። በአንዲት ቤተ ክርስቲያን (በአንድ ሲኖዶስ) ላይ የበላይ ሆኖ የሚሾም የሁሉም አባት ነው ። የሐዋ ሥራ 20 ፥ 28 ። በሕዝብና በካህናት ከተመረጠ በኋላ በዻሳሳት ይሾማል ። ፍት ነገ 5 ። ረስጣ 2 ። ፓትርያርክ ያወገዘውን ዻዻስ አይፈታውም ። መንፈሳዊ ሥልጣኑ ከሁሉም በላይ ነውና። (ሲኖ 51) ፓትርያርክ በመላዋ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ጊዜ ስሙ ይጠራል ።

ኤዺስ ቆዾስ

ዻዻስ በአንድ ሀገረ ስብከት አባት ሆኖ የሚሾም ነው ። ሲያገለግል በነበረበት አካባቢ ባሉ ምዕመናን ጥቆማና ድምጽ በርዕሰ ሊቃነ ዻሳሳቱና በሲኖዶስ ፈቃድ ይሾማል። (ፍት ነገ 5 : አብጥ 2) በአንድ ዻዻስ ብቻ አይሾምም። (ፍት ነገ 5 : ረስ 58 : ዲድ 34) ዻዻስ በሀገረ ስብከቱ በጸሎት ጊዜ ስሙ ይጠራል። (ፍት 5 : ክፍ 4)  አዲስ ጽላት ፣ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ፣ ይባርካል ። ለቄስ ለዲያቆን ሥልጣነ ክህነት ይሰጣል ። (1 ጢሞ 5 ፥ 2 : ፍት ነገ አን 5 ክፍ 4 )

ቀሳውስት

ቅስና የሚቀበሉት በዲቁና ክህነት በማገልገል ላይ ያሉ ሲሆኑ ፤ በሁለት መንገድ ይሾማሉ ።

  1.  በምንኩስና የተወሰነ ያላገባ ጌታን እንዴት እንደሚያገለግል የጌታን ነገር ያስባል ( 1 ቆሮ 7 ፥ 32 ) በማለት ቅዱስ ዻውሎስ እንደተናገረ ፤ በምንኩስና ለመኖር የፈለገ አስቀድሞ ወደ ገዳም ሄዶ የምንኩስናን ሕይወት መማርና አባቶችን እያገለገለ በተግባር ማየት አለበት ። በገዳም የሚሰጠውን አገልግሎት ከፈጸመ በኋላ ፤ አበምኔቱ ሲፈቅድለት ሥርዓተ ገዳሙ በሚያዝዘው መሠረት መዓርገ ምንኩስና ይቀበላል ። (ይመነኩሳል)ከምንከስና በኋላ ለክህነት የሚያበቃውን ትምህርት ተምሮ በየደረጃው ያሉትን የሥልጣነ መዓርጋት። በድንግልና ከመነኮሰና በትም ሕርቱም ሆነ በግብረ ገብነቱ በቂ ሆኖ ከተገኘ እስከ መጨረሻው የቤተ ክርስቲያን መዓርግ “ጵጵስና” ሊደርስ ይችላል ።
  2. በህግ የተወሰኑ ዲያቆናት በአንድ ህግ ከተወሰኑ ፤ በኋላ ለቅስና የሚያበቃ ትምህርትና ሥነ ምግባር ካላቸውና በሚያገለግ ሉበት አጥቢያ ሕዝብ ድምጽ ከተደገፉ ፤ ሊቀ ዻዻሱ ብቃታቸውን መዝኖ የቅስና መዓርግ ይሰጣቸዋል። (ፍገ ፡ 6)

ሰላሳ ዓመት ያልሆነው ቅስና አይሾምም ። ፍት ነገ ፡ 6 ። የቀሳውስት የአገልግሎት ድርሻ አስተምሮ ማጥመቅ ፤ ንስሐ መቀበልና መናዘዝ ፣ (ማሰርና መፍታት) ፤ ቀድሶ ማቁረብ ፤ ማስተማር…. ናቸው ።

ካህን የመጀመሪያ ሚስቱ ከሞተችበት ፤ መነኩሴም ምንኩስናውን ከተወው በኋላ የቅስና (የክህነት) ሥራ መሥራት አይፈ ቀድለትም ። ከማኅበረ ምዕመናን ግን አይለይም ።

ዲያቆናት

ዲያቆናት ካህናትን የሚራዱና የሚላላኩ ሲሆኑ ፤ በአገልግሎታቸው መሠረት የሚከተሉት ደረጃዎች አሏቸው

  1. ዲያቆን
    አስቀድሞ ሃይማኖቱን የተረዳ ፣ በምዕመናን ዘንድ በግብረ ገብነቱ የታወቀና የተመሰከረለት ፣ ለዲቁና አገልግሎት የሚያበቃውን ትምህርት ጠንቅቆ የተማረ ፤ ሆኖ ሲገኝ በአንብሮተ ዕድ (እጅ በመጫን) ይሾማል ። የተለየ ብቃትና ችሎታ ከሌለው በቀር ዕድሜው ከሃያ አምስት ዓመት በታች የሆነ ዲቁና አይሾምም ። ዲያቆን ከመጀመሪያ (ከህግ) ሚስቱ ከተፋታና ሌላ ካገባ ፣ ሃይማኖቱን ለውጦ በመናፍቃን ከተጠመቀ ፣ ከክህነቱ ይሻራል ። ፍት ነገ ፡ 7 ። ክፍል ፡ 5 ። ዲያቆናት መቅደስ ይገባሉ ፤ ነገር ግን መንበርና ታቦት ፣ (ከተለወጠ በኋላ) ሥጋውንና ደሙን በእጃቸው አይነኩም ። ዲያቆናት ለተልእኮ የሚፋጠኑ ፣ በትህትና የሚላላኩ ፣ በኑሯቸው ለሌላው አርአያ መሆን ይገባቸዋል ።
  2. ንፍቀ ዲያቆን
    የዲያቆን ረዳት ሲሆን ፤ መንፈሳዊ ሕይወቱ ፣ ግብረ ገብነቱና የሃይማኖቱ ጽናት በሚያገለግልበት አጥቢያ ካህናትና ምዕመናን የተመሠከረለት ። ፍት ነገ 8 ። ንፍቀ ዲያቆን በቃል ብቻ ይሾማል ፤ አንብሮተ ዕድ “እጅ በማጫን” አይደረግለትም ። ፍ ነ 8 ክፍ 2 ። የዲያቆን ረዳት እንደመሆኑ መጠን በሥራው ሁሉ ያግዘዋል እንጅ ንዋየ ቅድሳት አይነካም ። ፍት ነገ 8 ። ዶክ 45 ፣ 46 ። ጥፋት ሠርቶ ከተገኘ ከክህነቱ ይሻራል ። ፍት ነገ ፡ 8 ፡ ክፍል ፡ 4 ።
  3. አናጉንስጢስ
    አገልግሎቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጻሕፍት ማንበብ ሲሆን ፤ ትምህርቱና በግብረ ገብነቱ ከታየ በኋላ ተመ ርጦ ይሾማል ። ፍት ነገ 8 ክፍል1 ። አናጉንስጢስ አንብሮተ ዕድ አይደረግለትም በቃል ብቻ ይሾማል ። ፍት ነገ 8 ፡ ክፍ ፡ 2 ። በአገልግሎት ጊዜ ዲያቆናት በቅዳሴ ሠዓት የሚለብሱትን ልብሰ ተክህኖ አይለብስም ። ፍት ነገ 8 ፡ ክፍ 3 ። አናጉንስጢስ ጥፋት ከተገኘበት ከሥራ ታግዶ ከዓመት በኋላ ይመለሳል ። ከጥፋቱ ካልታረመ ከአገልግሎቱ ይሻራል ። ፍት 8 ክፍል 4 ። ሚስቱ ከሞተችበት ሌላ አግብቶ ማገልገል ይችላል ። ፍት ፡ 4 ፡ ክ ፡ 5 ።
  4. መዘምራን
    በቡራኬ ይሾማሉ ። ፍ ነገ ፡ 8 ክፍ ፡ 2 ። ከመዝሙረ ዳዊት ፣ በሀገራችን የቅዱስ ያሬድን ዝማሬም ይዘምራሉ ። በሚዘምሩበት ጊዜ ልብሰ ተክህኖ አይለብሱም ። ፍት ገነ ፡ 8 ክፍ ፡ 3 ። መዘምራን ሚስታቸው ከሞተችባቸው ሌላ ማግባት ይችላሉ ። ፍት ነገ ፡ 8 ክ ፡ 5 ። በሀገራችን መዘምራን ማለት የማኅሌት ትምህርት የተማሩትን ሲሆን ፤ እነዚህም ሥልጣነ ክህነት (ዲቁና ቅስና ፣ ከዚያም በላይ) ካላቸው በሁለቱም (በማኅሌትም በክህነታቸውም) ማገልገል ይችላሉ ። የሰንበት ት“ምህርት መንፈሳውያን ወጣቶችም መዘምራን ይባላሉ ።
  5. አጻዌ ኆኅት
    በቃል ብቻ ይሾማል አገልግሎቱ በር መክፈትና መዝጋት ሲሆን ልብሰ ተክህኖ አይለብስም ። ፍት ነገ 8 ፡ ክፍ ፡ 3 ። ሚስቱ ከሞተችበት ሌላ አግብቶ ማገልገል ይችላል ። ፍት ነገ ፡ 8 ፡ ክፍ ፡ 3 ።
  6. ሴቶች ዲያቆናውያት
    በትዳር ተወስነው የኖሩ ፣ ልጆቻቸውን በሥርዓት ያሳደጉ ፣ በቅዱስ ቁርባን የተወሰኑ ፣ ለአገልግሎት የ ሚፋጠኑ ፣ 8 ዓመት የሆናቸው ፤ ዲያቆዊት ሆነው በቃል ይሾማሉ ። 1 ጢሞ 5 ፥ 9 ። ፍት ፡ ነ 8 ፡1 ። ዲድ 17 ።አገልግሎታቸው

    • ከካህናቱ ወደ ሴቶች ይላላካሉ ፤ ሴቶች ክርስትና ሲነሱ ፤ ካህኑ እጃቸውን ይዞ ከአንገተችው በታች ቅብዓ ሜሮን ይቀባሉ ።
    • አይባርኩም ፤ ቄስና ዲያቆን የሚሠራውን የክህነት ሥራ አይሠሩም በሴቶች በር ቆመው ይቆጣጠራሉ ።
    • እንደ ዲያቆኑ ተንሥኡ ጸልዩ አይሉም ቅስና አይሾሙም ጉባዔ በጸሎት አይከፍቱም ። (ፍነ 8 ክፍ 1)

እነዚህም ፤ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ ከሌላው ምዕመን ተለይተው እነሱ ወደ ቤተክርስቲያን ስለቀረቡ ፤ ምዕመናን በሥጋ ድካም ቢሳሳቱ ፤ ከሚያገለግሉት ጓደኞቻቸው መካከልም የተሳሳተ ወንድማቸው ቢኖር ሊመክሩት ፤ ሊያጽናኑት ይገባል እንጅ ፤ የራሳቸውን ጽድቅ የወንድማቸውን ስህተት እያወሩ ፤ ለሚድኑት መሰናክል መሆን የለባቸውም። (ሉቃ 18 ፥ 9)