1  የጌታችን ትንሣኤ

ስለ ጌታችን ሞትና ትንሣኤ የተነገረ ትንቢት ፤ የተመሰለ ምሳሌ

ትንቢት

 • እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁ ፤ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርነቴ) ደግፎኛልና ነቃሁ ። መዝ 3 ፥ 5 ።
 • እግዚአብሔር ይነሣ ፤ ጠላቶቹም ይበተኑ ፤ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ ። መዝ 27 ፥ 1 ።
 • እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ ። መዝ 77 ፥ 65 ።

ምሳሌ

 • ዮናስ ፤ ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ማደሩ ፤ ለጌታችን ሞትና ትንሣኤ ምሳሌ ፤ እንደነበረ ጌታችን ተናግሯል ። ዮና 3 ፥ 1 ። ማቴ 12 ፥ 40 ።
 • በዮርዳኖስ ባህር ውስጥ ገብቶ መጠመቁ የሞቱ ፤ ከባህር መውጣቱ የትንሣኤው ምሳሌ ነበር ።

ጌታችን ዓርብ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ከለየ በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከዺላጦስ አስፈቅ ደው ዮሴፍ ለራሱ ባዘጋጃት መቃብር ከቀኑ በ11 ሠዓት ቀበሩት ።

ሥጋው ሶስት መዓልትና ሶስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ሲቆይ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄዶ በግዞት የነበሩ ነፍሳትን (አዳምን ከነልጆቹ) ወደ ቀደመ ቦታቸው ከመለሰ በኋላ ቅድስት ነፍሱንና ቅዱስ ሥጋውን በፈቃዱ አዋሕዶ ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ በ6 ሠዓት ተነሳ። መለኮት ግን(ሳይከፈል) ከነፍስ ጋር በሲኦል ፤ ከሥጋ (በመቃብር) ጋር አልተለየም ። ጌታችን በአካለ ነፍስ በሲኦል የቆየው (ዓርብ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት እስከ ቅዳሜ ሌሊት ስድስት ሠዓት) ለ32 ሠዓታት ያህል ነው ። በሥጋው 33 ዓመታት በምድር ፤ ነፍሱ ከሥጋው እስክትዋሃደችበትና እስከተነሳበት ጊዜ 33 ሠዓታት በሲኦል መቆየቱን እንረዳለ ።

ጌታችን ሶስት ቀንና ሌሊት በመቃብር ቆየ ማለት ዓርብ ከአስራ አንድ ሠዓት በኋላ ያለው እንደ ሃያ አራት ሠዓት ተቆጥሮ አንድ ቀንና ሌሊት ሲባል ፤ ዓርብ ማታና ቅዳሜ ቀን ሁለተኛ ቀንና ሌሊት ፤ የቅዳሜ ሌሊት ስድስቱ ሠዓት ከእሑድ ቀን ጋር ተቆጥሮ ሶስተኛ ቀንና ሌሊት ይሆናል።

ይህም በባህረ ሐሳብ ትምህርት መዓልት ይስህቦ ለሌሊት ፤ ወሌሊት ይስህቦ ለመዓልት ። ቀን ሌሊትን ፤ ሌሊትም ቀን ፤(የኋለኛው የፊተኛውን ፤ የፊተኛው የኋለኛውን) ይስበዋል ፤ በሚለው አቆጣጠር ነው።

የጌታችን ትንሣኤ ለሰዎች ትንሣኤ አብሳሪ(በኩር) ነው ። 1 ቆሮ 15 ፥ 20 ። እኛም እንደ እሱ ባለ ሞት (እርሱን በማመን ፀንተን) ከሞትን እንደ እርሱ ባለ የክብር ትንሣኤ ያስነሳናል ። ሮሜ 6፥5 ። ጌታችን ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ ከከሌሊቱ በ6 ሠዓት ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያት ሶስት ቀን ተገልጾላቸዋል ።

ይኸውም

 • በተነሳበት ቀን እሑድ ከቀኑ በ11 ሠዓት ደቀ መዛሙርቱ በዝግ ቤት ወስጥ ተቀምጠው እያሉ ተገለጠላቸው ። ሉቃ 24 ፥ 36 ። ዮሐ 20 ፥ 19 ።
 • በተነሳ በሳምንቱ እንደዚሁ በዝግ ቤት ውስጥ እንዳሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ በድጋሚ ተገለጠላቸው ። ዮሐ 20 ፥ 26 ።
 • በተነሳ በ25ኛው ቀን (ርክበ-ካህናት) ለሶስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ ተገልጦ ከእነሱ ጋር ማዕድ በላ ። ዮሐ 21 ፥ 1-14 ።

በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ሰባቱን ኪዳናት እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ ፤ መንፈስ ቅዱስን እስክልክላችሁ በኢየሩሳሌም ቆዩ ብሏቸው በአርባኛው ቀን በቢታንያ አደባባይ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ ፤ በአምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው ።

2  የሰው ልጆች ትንሣኤ

የሰው ልጆች ሁሉም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ ። ይሁንና እግዚአብሔር የወሰናት የምጽዓት (የዓለም ፍጻሜ) ቀን ስትደርስ ሁሉም ሰዎች ከሙታንነታቸው ህያዋን ሆነው ይነሳሉ ። ሲነሱ እኩሌቶቹ (ጻድቃን) ለክብር ፤ እኩሌቶቹ (ኃጥዓን)ለፍርድ(በሰሩት ክፉ ሥራ ሊፈረድባቸው) ነው ። ዮሐ 5 ፥ 29 ።

ስለ ሰው ልጆች ትንሣኤ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፥ ምሳሌ ተመስሏል

ትንቢት

 • ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ ፤ ሬሳዎችም ይነሳሉ ፤ ምድርም ሕያዋንን ታወጣለችና ። ኢሳ 26 ፥ 19 ።
 • በምድርም ዙሪያ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ ፤ እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሀፍረትና ጉስቁልና ይሄዳሉ ። ዳን 12 ፥ 1 – 3 ።
 • እርሱ ሰብሮናልና ይጠግነናል ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል ፤ በሶስተኛውም ቀን ያስነሳናል ። ሆሴ 6፥2 ።

ምሳሌ

 • የአቤል ሞት ለሞታችን ። ዘፍ 4፥ 8 ። የሄኖክ ዕርገት ለትንሣኤያችን ። ምሳሌ ነው ። ዘፍ 5 ፥ 24 ።
 • እስራኤል ወደ ግብጽ መውረዳቸው ለሞታችን ። ዘፍ 46 ፥ 1 ። ከግብጽ ወጥተው ከነዓን መግባታቸው ለትንሣኤያችን ምሳሌ ነው ። ግብጽ የመቃብር ፤ ከነዓን የትንሣኤ (የመንግስተ ሰማያት) ምሳሌ ናትና ። ዘፀ 14 ፥ 21 ።
 • የአልዓዛር ሞቱ ለሞታችን ፤ በአራተኛው ቀን መነሳቱ ለትንሳኤያችን ምሳሌ ነው ። ዮሐ 11 ፥ 1- 44 ። ሌሎችም ትንሣኤ ሙታንን የሚያመለክቱ በርካታ ምሳሌዎች አሉ ።

ሰው የተፈጠረው እንዲሞት ሳይሆን በሕይወት እንዲኖር ነበር ። ይሁን እንጅ በቃኝን በማያውቀው ፍላጎቱ የተሰጠው ሥልጣን አልበቃ ብሎት በዕባብ ውስጥ ባደረው በሰይጣን ምክር ተታሎ ፤ ያልተሰጠውን አምላክነት ሲፈልግ በመገኘቱ ሞት ተፈረደበት ። በአንዱ ሰው አዳም በደል ምክንያትም ሞት ወደ ዓለም መጣ ። ሮሜ 5 ፥ 12 ። በአዳምና በልጆቹ (በሰው ዘር ሁሉ) ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ሁለት ማለትም ሞተ ነፍስና (ወደ ገሃነም መውረድ) ሞተ ሥጋ (ወደ መቃብር መውረድ) ሲሆን ሞተ ነፍስ አምላካችን ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙና በቆረሰው ሥጋው ስለተደ መሰሰ አምነው ከተጠመቁ በኋላ ይህን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለሚቀበሉ ምዕመናን ቀርቶላቸዋል ። የሥጋ ሞት ግን ሁሉም ሰዎች እስኪጠናቀቁ ግዛቱ ይቀጥላል ፤ ሁሉንም ይገዛ ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶታልና ። 1 ቆሮ 15 ፥ 26 ።

የሙታን አነሳስ

ሙታን ከመነሳታቸው በፊት መልአኩ 3 ጊዜ የመለከት አዋጅ (ንፍሐተ ቀርን) ያሰማል ። 1 ተሰ 4 ፥ 16

በመጀመሪያው (ንፍሐተ ቀርን) የመለከት ድምጽ የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ የሰውነት ክፍላቸው በሙሉ ይሰባሰባል ።

በሁለተኛው የመለከት አዋጅ ፦ የሰውነት ክፍሎቻቸው ከደምና ከሥጋ ጋር ተገጣጥመው የማይንቀሳቀስ በድን ይሆናሉ ።

በሶስተኛው የመለከት አዋጅ ፦ የሰው ልጆች ሁሉ በሕይወት ዘመናቸው የሠሩትን መልካምም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ፤ ወንዶች የሰላሳ ፤ ሴቶች የአስራ አምስት ዓመት ዕድሜ ያህል ሆነው ይነሳሉ ። ሲነሱም ጻድቃን ፈጣሪያቸውን ክርስቶስን መስለው ፤ ኃጥዓንም አለቃቸውን ዲያብሎስን መስለው ይነሳሉ ።

ከዚህ በኋላ ጌታችን በክበበ ትስብዕት (በለበሰው ሥጋ እየታየ) በግርማ መነግሥት (በሚያስፈራ የመለኮት ግርማ) ሆኖ በመላእክት ታጅቦ የተሰቀለበትን መስቀል ፊት ለፊቱ አደርጎ ይመጣል ። መስቀል የፍርድ ምልክት ነውና በዚህ ጊዜ በቀራንዮ አደባባይ በግፍ ሰቅለው የገደሉት አይሑድ ያፍራሉ ። ማቴ 25፥31 ።

ጌታችን ፤ ጻድቃንን በበግ ፥ ኃጥዓንን በፍየል ይመስላቸዋል

ይህም ማለት የሰውነት ባህርያቸው ተለውጦ በጎችና ፍየሎች ይሆናሉ ማለት ሳይሆን በሕይወት ዘመናቸው በዚህ ዓለም ሲኖሩ የሰሩት ሥራቸው በበጎችና በፍየሎች ምሳሌ ሆኖ ስለቀረበ ያንኑ ለማስረዳት ነው ።

በጎች፦ እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ረግተው ይውላሉ፤ ጻድቃንም እውነተኛ እረኛቸው ክርስቶስ በሰራላቸው ህግ ጸንተው ይኖራሉና ። ዮሐ 10 ፥ 1 ። ዮሐ 21 ፥ 15 ።

ፍየሎች ፦ ለእረኛ አስቸጋሪዎች ናቸው ፣ በአንድ ቦታ መርጋትም አይችሉም ። ኃጥዓንም በተፈቀደላቸው ህግ አይኖሩም ወረተኞች ቀላዋጮች ናቸው ።

በጎች ፦ ጥቂት ሳር ካገኙ ተስማምተው ይበላሉ ። ጻድቃንም ኑሮዬ ይበቃኛል ፡ በማለት ያለቻቸውን ከድሆች ጋር ተካፍለው ይበላሉ ።

ፍየሎች ፦ የሚበሉት ሳሩ ቅጠሉ እያለ እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ ፤ ሲያጉረመርሙ ይውላሉ ። ኃጥዓንም ሁሉ እያላቸው ሲጣሉ ሲካሰሱ ፤ ሲገዳደሉ ፤ የሌላውን ሲመኙ ፤ ሲሰርቁ ፤ ይኖራሉ ።
የበጎች ፦ ኀፍረተ ሥጋቸው በላታቸው የተሸፈነ ነው ። የጻድቃንም ኃጢዓታቸው በንስሓ የተሰወረ ነው ።

የፍየሎች ፦ ኀፍረተ ሥጋቸው የተገለጠ ፤ ላታቸው የተሰቀለ ነው ። ኃጥዓንም ነውራቸው ለሁሉ የተገለጠ ኀፍረት የሌላቸው ደፋሮች ፤ በነውራቸውና በክፉ ሥራቸው የሚመኩና የሚኩራሩ ፤ ናቸው ።
በጎች ፦ ሲሄዱ አንገታቸውን ወደ ታች አቀርቅረው ነው ፤ ጻድቃንም ሲኖሩ አንገታቸውን ደፍተው ራሳቸውንዝቅ አድርገው በትህትና ነው ።

ፍየሎች፦ ሲሄዱ አንገታቸውን አቅንተው ሽቅብ እያዩ ነው ፤ ኃጥዓንም ሲኖሩ ከአቅማቸው በላይ በማሰብ በትዕቢት ተወጥረው ፤ ከእኛ በላይ አዋቂ ለኀሳር እያሉ የሌላውን ሥራ በማኮሰስ ነው ።

በጎች ፦ ከጓደኛቸው አንዱን ተኩላ ፡ ቀበሮ ፡ ከበላባቸው ፡ አካባቢውን ለቀው ይሄዳሉ ፡ በረው ይጠፋሉ ። ጻድቃንም ከመካከላቸው አንዱ በሞት ቢነጠቅ ነገም ለእኛ ብለው ራሳቸውን ለንስሐ ያዘጃሉ

ፍየሎች ፦ ከጓደኛቸው አንዱን አውሬ ቢነጥቀው ለጊዜው ዘወር ይሉና ፥ በኋላ ረስተውት ተመልሰው በአካባቢው ሳሩን ቅጠሉን ሲበሉ ይገኛሉ ። ኃጥዓንም ከመካከላቸው አንዱ በሞት ሲነጠቅ ለጊዜው ያዘኑ ይመስሉና ጥቂት ቆይተው የሞተውን ሰውዬ ረስተውት ፤ ጥሎት በሄደው በሃብቱና በንብረቱ ሲጣሉ ሲካሰሱ ይታያሉ ።

ጌታችን ለፍርድ ሲቀመጥ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥዓንን በግራው ያቆማቸዋል ። ማቴ 25 ፥ 31 ።

ምሳሌነቱም ፦

 • ቀኝ ፈጣን ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ፈጣኖች ፡ ትጉኃን ናቸውና ።
 • ግራ ዳተኛ ነው ። ኃጥዓንም ለመልካም ነገር ዳተኞች ናቸው ፤ አይመቻቸውም ።
 • ቀኝ ከግራ ይልቅ ጠንካራ ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ብርቱዎች ናቸው ።
 • ግራ ከቀኝ ይደክማል ። ኃጥዓንም ጹሙ ጸልዩ ሲባሉ ፣ አይችሉም ይሰንፋሉ ።
 • ቀኝ ለሥራ ይመቻል ቀና ነው ። ጻድቃንም ለበጎ ነገር ቅኖች ናቸውና ።
 • ግራ ጠማማ ነው ለሥራ ብዙም አይመችም ። ኃጥዓንም ሃሳባቸው የተወላገደ ፤ በቃላቸው የማይገኙ ፤ በባህርያቸው ተለዋዋጮች ናቸው ።

ጌታችን ለፍርድ የሚመጣባት ቀን መቼ እንደሆነች ማንም አያውቃትም ። በማቴ 24 ፥ 36 ። ወልድም ቢሆን አያውቃትም የሚለው ግን በእግዚአብሔር የሶስትነት (ከዊን ኩነት) ሁኔታ ውስጥ ፤ አብ ልብ ስለሆነ ፤ በአብ ልብነት ዓለም እንደምታልፍ ታስባለች ፤ ትታወቃለች ። ወልድ ቃል ስለሆነ ፡ ትለፍ ብሎ በቃልነቱ አላወቃትም ፤ ተናግሮ አላሳለፋትም ፤ በድርጊት አልፈጸማትም ማለት ነው ። ከትንሣኤ ሙታን በኋላ ፤ ሰማይ (ጠፈር) ፤ ሶስቱ ሰማያት ፤ ኢዮር ፤ ራማ ፤ ኤረር ፤ ሲኦል ፤ ገነት ፤ አራቱ ባህርያት ፤ መሬት ፤ ውሃ ፤ እሳት ፤ ነፋስ ፤ እንስሳት ፤ አራዊት ፤ አእዋፍ ፤ ያልፋሉ ። ብርሃንና ጨለማ አያልፉም ከ24 ሰዓት ውስጥ ሌሊቱ /ጨለማ ወደ ገሃነመ እሳት ፤ ቀኑ /ብርሃን ወደ መንግስተ ሰማያት ይጠቃለላሉ ። አራቱ ሰማያት ፤ ጽርሐ አርያም ፤ መንበረ መንግስት ፤ ሰማይ ውዱድ ፤ መንግስተ ሰማያት ፤ (ኢየሩሳሌም ሰማያዊት) ፤ ገሐነመ እሳት ፤ ግን አያልፉም ፤ ለዘለዓለም ይኖራሉ ። ማቴ 24 ፡35

በመጨረሻም ጻድቃንን “እናንት የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ” ብሎ ከቅዱሳን መላእክት ጋር መንግስተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል ። ማቴ 22፥30 ። ኃጥዓንንም “እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል ። ከዚህ በኋላ የዘለዓለም መኖሪያቸው ከግብር አባታቸው ከዲያብሎስና ከአጋንንት ጋር የፍርድና የስቃይ ቦታ በሆ ነው በገሐነመ እሳት ይሆናል ። ራዕ 12 ፥ 7 ።

በመንግስተ ሰማያት የሚኖሩ ጻድቃን በምድራዊ ሕይወታቸው እያሉ በሠሩት ሥራ የተለያየ ክብር ቢኖራቸውም ፤ በሥልጣን ግን አንዱ ከአንዱ አይበልጥም አንዱ ሌላውን አያዝዘውም ። 1 ቆሮ 15፥41 ።

ሙታን የሚነሱት በማይፈርስ ፤ በማያረጅ ፤ በማይራብ ፥ በማይደክም ፤ በማይሞት ፤ ሥጋ ነው ። 1 ቆሮ 15 ፤ 42 ። በመንግስተ ሰማያት ፤ ጋብቻ የለም ፤ ሁሉም በዚህ ዓለም ያበቃል ። ማቴ 22 ፥ 30 ።