ተክሊል ከለለ ፤ ጋረደ ። ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ተክሊል ማለት ፤ መከለል ፣ መወሰን ፣ መጋረድ ፣ መለየት ፣ ማለት ሲሆን  በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለሚጋቡ ምዕማናን የሚፈጸምላቸው ሥርዓት ነው። እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ ምድርን ሙሏት ብሎ አዘዛቸው።(ዘፍ 1 ፥ 27)  ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሴትና ወንድ በጋብቻ እየተሳሰሩ ልጆችን በመውለድ መባዛት ጀመሩ ።

የጋብቻ ዓላማዎች

  1. ለመረዳዳት ፤ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ አግባብ አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ። ዘፍ 2 ፥18 ።” ብሎ እግዚአብሔር እንደተናገረ ፤ ሰው በኑሮው ሁሉ እንዳይቸገር የውስጡን ሀሳብ የሚያካፍለው ፣ ችግሩን የሚጋራውና ራሱን የሚወክልለት የህይወት አጋሩን እየመረጠ ጋብቻ ይመሠርታል ።
  2. ለፈቃድ ፤ ሰው በባህርዩ ፍትወት (የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት) አለበት ። ሰለሆነም በጋብቻ ተወስኖ እንዲኖርና ከፈተና እንዲጠበቅ ተፈቅዶለታል ። 1ቆሮ 7 ፥ 2-38 ። እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻም መኝታው ንጹህ ነው ተብሏል ። ዕብ 13 ፥ 4 ።
  3. ለመባዛት ፤ ዛሬ በዓለማችን የምናየው የሕዝብ ቁጥር የተጀመረው በአንድ አዳምና በአንዲት ሄዋን ከተመሠረተ ህጋዊ ጋብቻ ነው ። ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ብሎ የተናገረውና የፈቀደው እግዚአብሔር ስለሆነ እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በዚሁ መንገድ ልጆች ይወለዳሉ ። ዘፍ 1 ፥ 27 ።
  4. ከጋብቻ በፊት

የተጋቢዎቹ ስምምነትአስቀድመው በጋብቻው ሁለቱም ተጋቢዎች መተወዋቅ መስማማትና መወሰን አለባ- ቸው ። ትዳርን ያህል ታላቅ ነገር በሌሎች ግፊትና ትእዛዝ መወሰን የለበትም ። እጮኛሞች ሲተዋወቁም በስህተት ውስጥ ወድቀው ሃይማኖታቸውን እንዳያስነቅፉ ግንኙነታቸው ከዓለማውያን ሰዎች ልዩ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም ። በመጠናናትም ጊዜ ማለፍ የለበትም ጊዜ በረዘመ ቁጥር ሃሳብ ይለዋወጣልና ።

የሃይማኖት አንድነት ፤ለጊዜው ቀላል መስሎ የሚታየው የሃይማኖት ጉዳይ ፣ በኋላ ለመፍታት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ። በአንድ ሃይማኖት የሚያምኑና ሥርዓቱን ጠብቀው የተጋቡ ከሆኑ ግን እንደ አንድ ያስባሉ ሳይነጋገሩም በሀሳብ ይስማማሉ ፣ ይተሳሰባሉ….. ። በእርግጥ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነውን አስተምሮ አሳምኖ ማግባት ይፈቀዳል ። ነገር ግን እሰብካለሁ ሲሉ መሰበክ እንዳይመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ።

የአእምሮና የአካል ብስለት ፤ እንደ ቤተ ክርስቲያ ትምሕርት የጋብቻ ዕድሜ ፣ ሴት ከአሥራ አምስት ፤ ወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ሲሆን ፤ የአእምሮ ዝግጅት ማለትም ፤ ከሃይማኖት አንጻር ፡ ስለ ትዳር መማርና መረዳት ፣ ከትዳር በኋላ ስለሚኖረው ህይወት ግንዛቤ ማግኘት ፣ ከጋብቻ በኋላ ከትዳር ጓደኛው የሚቀርበው ሰው እንደሌለ ማወቅ ፣ ራስን ለትዳር ጓደኛ አሳልፎ ለመስጠት መወሰንና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በትዕግሥት ለማሳለፍ መዘጋጀት ናቸው ።

በጋብቻ ጊዜ

በውሳኔ መጽናት ፤ የሁለቱም ወገን ዘመዶችና ጓደኞች የራሳቸው ፍላጎት እንዲሆንላቸው በማሰብ ፤ ስለ ሠርጉ ፕሮግራም በማውጣት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዲደረግ ፣ ወይም ደግሞ በሁለቱም በቤተ ክርስቲያንም (በሥርዓተ ተክሊል እንዲፈጸም በመዘምራን እንዲታጀቡ) እንደገናም ፤ በዓለማዊ ሠርግ (በቬሎ እንዲወጡ ፣ በባንድ እንዲታጀቡ) በማዋከብ ግራ ሊያጋቡ ይችላሉ ። ነገር ግን የሚጋቡት አጃቢዎቹ ስላልሆኑ ፣ መወሰን ያለበት በሙሽሮቹ ነው ። ሙሽሮቹም በውሳኔያቸው መጽናት አለባቸው ። በውስጣቸው ያልተቆረጠ ዓለማዊ ፍላጎት ስላላቸውና ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ለቤተሰቦቻቸው ምክርና ትእዛዝ ክብር በመስጠት ሠርጉ የተደበላለቀና ቅጥ ያጣ ፤ ብዙ ሰዎችንም የሚያሰናክል ሊሆን አይገባም ።

ጋብቻው በቅዱስ ቁርባን መሆን አለበት ፤ሥርዓተ ተክሊል የሚፈጸምላቸው የሥጋ ድንግልና ላላቸው ሲሆን ሌሎችም ክርስቲያኖች ጋብቻቸውን በቅዱስ ቁርባን ማድረግ ይችላሉ ። ክርስቲያናዊ ጋብቻ ያለ ቅዱስ ቁርባን አይደረግም ። አንዳንድ ሰዎች ፤ ለፎቶ ግራፍና ለቪዲዮ ሲሉ ብቻ ፣ ጋብቻቸውን በሥርዓተ ተክሊል ለማድረግ ያስባሉ ፣ ይህ ተገቢ ስላልሆነ አስቀድመው ስለ ጋብቻ ትምህርት በሚገባ መማርና ምርጫቸውን ከወዲሁ ማስተካከል ይገባቸዋል ።

ከጋብቻ በኋላ

ስምምነቱ ተጠብቆለት ሳይሆን በተፈጥሮ ህግ ነው ። እናትና አባቱን ይቀበላል እንጅ ለመቀበል ድርድር ውስጥ አይገባም ። ከእኛ በፊት የተደረጉ ነገሮችን በሙሉ አምነን እንድንቀበል ተፈጥሮ ያስገድደናል ። ትዳር ግን ተስማምቶ ወዶና ፈርሞ የሚገባበት ዘላቂ ሕይወት ስለሆነ ስምምነቱ እስከ ሕይወት ፍጻሜ የጸና ነው ። “ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ወደ ሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ይሆናሉ” ። ዘፍ 2 ፥ 24 ። ማቴ 19፥4 ። ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት በትዳራቸው ውስጥ ማንም ሊገባ አይፈቀድለትም ።

ወላጆችም ቢሆኑ ልጆቻቸው ባይስማሙ ያስታርቃሉ ይመክራሉ እንጅ ለእነሱ ስላልተስማማቸውና ግላዊ ጥቅማቸው ስለቀረባቸው ብቻ ፍታት ፍቺው እያሉ የልጆቻቸውን ትዳር መበጥበጥ የለባቸውም የብዙዎች ትዳር የሚበተነው በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት በመሆኑ ባለትዳሮች ይህን ጉዳይ አስቀድመው ሊረዱት ይገባል:: ባልና ሚስት አንድ ስለሆኑ በመካከላቸው ሁለትነት መታየት የለበትም ፤ ሰው ከቤተ ሰቡ ጋር የተዛመደው

ፍቺ የሚፈቅድባቸው ምክንያቶች

  1. ሞት
    ከሁለቱ አንዳቸው በሞት ቢለዩ በሕይወት የቀረው ሌላ እንዲያገባ ተፈቅዶለታል ። ነገር ግን ጋብቻው በአንድ ሃይማኖት ከሚኖሩና በቅዱስ ቁርባን መሆን አለበት ። ሮሜ 7፥ 2 ። 1 ቆሮ 7 ፥ 39 ።
  2. የጤና ጉድለት
    በትዳር ለመኖር እስከማይችሉበት ድረስ በእንዳቸው ላይ የጤና(በጾታዊ አካላቸው ላይ) ችግር ካገጥማቸውና ለአብረው ለመኖር ካልተስማሙ መፋታት ይችላሉ ። ምክንያቱም ከጋብቻ መሠረታዊ ፍላጎቶች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ስለተጓደለ ካልተስማሙ በቀር አብረው ለመኖር አይገደዱም ።
  3.  የሃይማኖት ልዩነት
    አንዳቸው ከኦርቶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ወጥተው የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑና ተመክረው መመለስ ካልቻሉ በሃይማኖቱ የጸናው ትዳሩን መፍታት ይፈቀድለታል ። ነገር የተለየው ተመልሶ ካመነና ይቅርታ ከጠየቀ የትዳር ጓደኛውም ይቅርታውን ከተቀበለውና ከተስማማ በትዳራቸው መቀጠል ይችላሉ ።
  4. ዝሙት
    ከሁለቱ አንዳቸው በዝሙት ከወደቁ እና ከጥፋታቸውም መታረም ካልቻሉ ፤ ንጹሁ ሰው ትዳሩን መፍታት ይችላል ። ነገር ግን ወሬ በመስማትና በጥርጣሬ መሆን አለበት ። ማቴ 5 ፥ 32 ። የቤትን ገመና ለውጭ ማውራት ነገረ ሰሪ የሆኑ ሰዎችን ሊያስገባ ይችላልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። የትዳር መሠረቱ በእውነት መግባባትና መተማመን ስለሆነ በሁኔታዎች መጠራጠርና መጨቃጨቅ አያስፈልግም ።

በዝሙት ኃጢአት የወደቀ የትዳር ጓደኛውም ከስህተቱ ተመልሶ ንስሐ ከገባና ይቅርታ ከጠየቀ ፤ እንደ በፊቱ በትዳራቸው መቀጠል ይችላሉ ። ባልና ሚስት በትዳራቸው በሚኖረው ማንኛውም ዓይነት ኑሮ በመመካከርና በመወያየት መወሰን አለባቸው ። ትዳር ፡ የሁለቱም የጋራ ሕይወት ስለሆነ ፤ መመሪያ አውጪና ተቀባይ መሆን የለባቸውም ። ገቢያቸውም ሆነ ወጪያቸው በጋራ መ ወሰን አለበት ። ትዳሩ እውነት የሚሆነው እነዚህ ሲሟሉ ነውና ።

የባለትዳሮችን አንድነት የበለጠ የሚያረጋግጡት የሚወልዷቸው ልጆች ናቸው ልጆች የሁለቱም እኩል ሀብቶች ስለሆኑ ያቀራርቧቸዋል ። ትዳራቸውንም ማክበር ያለባቸው የሚወዷቸው ልጆቻቸው እንዳይበታተ-ኑባቸው በማሰብ ጭምር መሆን አለበት ። በመካንነት ምክንያት መውለድ ያልቻሉት ባለትዳሮችም እግዚአብሔር ለእነሱ የወሰነላቸው የተሻለ መሆ ኑን በማሰብ ማመስገን ይገባቸዋል እንጅ በአምላክ ሥራ ገብተው ማማረር አይገባቸውም ። የተወለደውም ቢሆን ካልተባረከ ሊሞት ወይም መጥፎ ልጅ ሊሆን ይችላል ። እግዚአብሔር አውቆ ያደረገውን አምላካዊ ጥበብ ባለማወቅና ያሰቡት ስላልተሳ ካላቸው ብቻ ራሳቸውን የተረገመ አድርገው መቁጠር የለባቸውም እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለበጎ ነው ብሎ መቀበል ይገ ባል ። ገና ከማያውቋቸውና ካልተወለዱ ልጆች ይልቅ የሚወዱትና ከእግዚአብሔር አደራ የተቀበሉት የትዳር አጋራቸው እን ደሚበልጥባቸውም በማስተዋል ማሰብ ይገባቸዋል። (ዘፍ 30 ፥ 1)